የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ መንግስት ለመቀየር የሚደረግን ሙከራ በመቃወም ለአፍሪካ ህብረት ደብዳቤ ፃፈ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ300 በላይ አባላት ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ መንግስት ለመቀየር በድብቅ የሚደረግን ሙከራ በመቃወም ለአፍሪካ ህብረት ግልጽ ደብዳቤ ፃፈ።
ጥምረቱ ለወቅቱ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፌሌክስ ሺሴኬዲ በጻፈው ደብዳቤ፥ በኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ የሃይል እርምጃና ሴራ ለመቀየር የሚደረገውን ሙከራ የአፍሪካ ህብረት እንዲያወግዝ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፥ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መስራች አባል አገር እና የህብረቱ መቀመጫ መሆኗን ጥምረቱ በደብዳቤው አስታውሷል።
የአፍሪካ ህብረትም በአባል አገራቱ ውስጥ ከሕገ መንግስታዊ ስርዓት ውጪ ስልጣን መያዝን የመከላከል፣ የማውገዝና ያለመቀበል ግዴታ እንዳለበትም ነው ጥምረቱ በደብዳቤው የጠየቀው።
ኢትዮጵያውያን ባለፈው ሰኔ ወር ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ በማካሄድ ይበጀናል ያሉትን አካል መምረጣቸውንም ጠቅሷል።
ከዚህ በተቃራኒው ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ አሸባሪው ህወሓት እና ምዕራባውያን መንግስትን ለመቀየር ሙከራ ማድረጋቸው ህገ ወጥ መሆኑን ይገልጻል ደብዳቤው።
ከዚህ ባለፈም የአሸባሪው ህወሓት መሪዎችና የአጋሮቹ ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በድብቅ መንግስትን በመጣል የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ሲያሴሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መውጣቱንም በማሳያነት ተጠቅሷል።
አንዳንድ የውጭ አገራት የሽብር ቡድኑን ሲደግፉ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በሃይል ለማስወገድ ሲያሴሩ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ ተመድ ድርጊቱን የሚቃወም መግለጫ አለማውጣታቸውንም ጠቁሟል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ከ300 በላይ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን በውስጡ ያቀፈ ነው።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!