Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሀገራቸውን ዳር ድንበር አሳልፈው አይሰጡም-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ጋር በተርጫ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም ለተሰባሰበው የአካባቢው ነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሀገራቸውን ዳር ድንበር አሳልፈው አይሰጡም ብለዋል።

ዳውሮዎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶቻቸው ጋር ተደምረው አገራቸውን ወደሚገባት የብልጽግና ማማ እንዲያወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቅርበዋል።

በንግግራቸውም የዳውሮ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በጦር አውድማ የተዋደቀ ጀግና ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል።

አስደናቂ ታሪክና የተፈጥሮ ሃብት ካላቸው የዳውሮ ሕዝቦች ጋር ለመኖር ‘ከአራቱም አቅጣጫ ያልመጣ ኢትዮጵያዊ የለም’ ብለዋል።

ዳውሮዎች ስጋን አልፎ አጥንት የሚነቀንቅ /ድንቄ/ የሚባል የሙዚቃ መሳሪያ፤ ከቻይና ግንብ ያልተናነሰ የኬላ ሃላላ የድንጋይ ካብ ባለቤቶች ስለመሆናቸውም መስክረዋል።

ተካፍሎ መብላት ብቻ ሳይሆን ተካፍሎ መምራት የሚችሉ በመሆናቸው ይህን ልምድ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

ዳውሮ ቤተኝነት እንጂ እንግድነት፤ ባለቤትነት እንጂ መጤነት የሌለበት በመደመር የሚያምን ሕዝብ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዳውሮ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የብልጽግና መንገድ ሠላም፣ ይቅርታና ፍቅር በመሆኑ ከሌሎች ጋር ተደምሮ ወደ ብልጽግና ማማ ማውጣት አለበት ብለዋል።

የዳውሮ ዞን አስር ቀበሌዎችና የተርጫ ከተማ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ 177 ሰንጋ፣ ፍየልና ቅቤ እንዲሁም የዳውሮ ዲንኬ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ በስጦታ እንዳበረከቱላቸው ኢዜአ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስር ዶክተር ዐቢይ  በዛሬው ዕለት ከዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪየ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ድህነት እንዴት መከፋፈልን እንደሚያስከትል በመግለጽ በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ጀግንነት በአንድነት ሆኖ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ እና ኢትዮጵያን ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿ የኃይል ምንጭ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስካሁን በተለያዩ ዘርፎች ላከናወኗቸው ስኬታማ ስራዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ሴት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ሴቶችን ከፍ በማድረግ እና ወደፊት በማምጣት ላከናወኑት ስራ ምስጋና ማቅረባቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ነዋሪዎች በዞኑ የሚስተዋሉ የውኃ አቅርቦት፣ ከከተሞች ዕድገት ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች መጓተት ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የዳውሮ ቅርሶች እንዲመዘገቡ የማድረግ እንቅስቃሴ እንዲጀመር፣ የኦሞ ሸለቆ እሴቶች ላይ የሚያተኩር ጥናት እና ምርምር እንዲካሄድ እና የቀርከሃ ኢንዱስትሪ ተፈጥሮ ለሥራ ዕድል እንዲውል ጥያቄ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምላሻቸው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በቅርቡ የሚጀመረው የ10 ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ ቁልፍ ይዘቶች በዳውሮ ነዋሪዎች የተነሱትን ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ለመመለስ የሚያስችል አካሄድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.