ሩሲያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አደነቀች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደምታደንቅ ገለጸች፡፡
በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገራት ግንኙነት ጉዳይ ምክትል ዳይሬክተር አይቨን ነካይቭ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ለዚህም መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተናጠል ተኩስ ለማቆም መወሰኑን፣ ተጥሎ የነበረውን የአስኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱን፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን እና ከህወሓት ጋር ለሚደረገው ሰላማዊ ውይይቱ ኮሚቴ ማዋቀሩን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት ፍኖተ ካርታ እንዳዘጋጀ መግለጻቸውን ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ÷ ሩሲያ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳየውን ተነሳሽነት እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ እንዲዳረስ እና የተጎዱ መሰረት ልማቶች እንዲገነቡ የሚያደርገውን ጥረት እንደምታደንቅ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት መር ለሚደረገው የሰላም ውይይትም የሩሲያ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን በኢትዮጵያ ከሩሲያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡