ወጣቶች በሥራ ላይ የሚያተኩሩ፣ የሀገራቸውን ጸጋ የሚያለሙ እና ፈጣሪያቸውን አመስጋኝ መሆን አለባቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶች በሥራ ላይ የሚያተኩሩ፣ ሀገራቸውን ለማወቅ የሚተጉ፣ የሀገራቸውን ጸጋ የሚያለሙ እና ፈጣሪያቸውን አመስጋኝ መሆን አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሐፍ÷ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ትልቅ እንደ ነበረች አስታውሰው ወደ ቀደሞ ከፍታዋ እንድትመለስ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማጽናት የዚህች ድንቅ ሀገር ልጆች ግዴታ ነው ብለዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ከመላው አገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር እየተወያዩ ነው፡፡
በውይይታቸውም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
የወጣት ተወካዮች የመጡባቸውን አካባቢዎች መሠረት በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከወጣት ተወካዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ።
የውይይት መድረኩ መሰረታዊ የሆኑ የወጣቶችን ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡