የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ በተደረገው ርብርብ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል- አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል እና የመቀንጨርን ችግርን ለመቅረፍ በተደረገ ርብርብ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
የ2014 በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት የከፍተኛ አመራር መድረክ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የሰቆጣ ቃል ኪዳን አፈፃፀም የከፍተኛ አመራር መድረክ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።
አቶ ደመቀ ባለፉት ዓመታት የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ እና መሰረታዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮግራሞች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በተለይ ለሰቆጣ ቃልኪዳን ተፈፃሚነት በሶስት ምዕራፍ የተከፈለ የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ በማድረግ አዋጪና ዘላቂነት ያለው ርብርብ መደረጉንም አብራርተዋል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳንን በተሟላ አግባብ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚመለከታቸው ቁልፍ የፌዴራል ተቋማት መካከል የተቀናጀ አሰራር ስርዓት መዘርጋቱ ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ጠንካራ መሰረት መጣሉን አስረድተዋል፡፡
የተቀናጀ አሰራር ስርዓት መዘርጋቱ የመቀንጨርን ችግር ለመቅረፍ የተከናወኑት ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደመቀ በጦርነት እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በሚገኙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ወገኖችን በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ወደፊት የቅንጅት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመሰል ሀገራዊ ፕሮግራሞች የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ሰላም በሁሉም አካባቢዎች ማረጋገጥ መንግስት ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሰጠው እና በቁርጠኝነት ተፈፃሚ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።