በዜግነት አገልግሎት ነፃ የህክምና አገልግሎት በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዜግነት አገልግሎት ነፃ የጤና ምርመራ እና የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራ ‘’በጎነት ለጤናችን’’ በሚል መሪ ቃል በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል መሰጠት ተጀመረ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተርዮሐንስ ጫላ እንደገለጹት÷ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ዕድሜአቸው ከ50 ዓመት በላይ ለሆኑ አቅመ ደካሞች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ነፃ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በከተማዋ በሚከናወነው የዜግነት አገልግሎት 17 ሺህ አቅመ ደካሞች የተለያየ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ÷ በዜግነት አገልግሎት በሀገር ደረጃ ለ100 ሺህ አቅመ ደካሞች የነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ ነውብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በሐረሪ ክልል “በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል ነጻ የህክምናና የምርመራ አገልግሎት መስጠት በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡
መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የተጀመረው መርሐ ግብርም መክፈል የማይችሉ ዜጎች በነፃ የህክምናና የምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ መሰል የበጎ ፈቃድ ተግባራት በሌሎች ዘርፎች ላይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው÷ ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎቱ አቅመ ደካማ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ 5 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!