Fana: At a Speed of Life!

ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ የተፈናቃዮች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አቶ አሻድሊ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዕምቅ ተፈጥሮ ሀብት መኖሩን ጠቅሰው÷ ይሁን እንጂ  የነበረው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማስከተሉን አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለመመለስና ለማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትንና ፕሮጀክቶችን መልሶ ለመገንባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም  በተሳሳተ መንገድ ወደጦርነት ገብተው የነበሩና በሠላማዊ መንገድ የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ የተደራጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተካሔደው የዳሰሳ ጥናት መሠረት በመተከል፣ ካማሺና አሶሳ ዞኖች እንዲሁም ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ በጸጥታ ችግሩ የተከሰተው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ የዕርዳታ ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉም አቶ አሻድሊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ አሻድሊ በዓለም አቀፍ የተፈናቃዮች ድርጅት ለታቀደው የፕሮጀክት ትግበራ ስኬት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከ457 ሺህ በላይ ዜጎች  ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን÷ 189 የጤና ተቋማት፣ 221 ትምህርት ቤቶች፣ 1 ሺህ 390 የውኃ ተቀቋማት፣ 360 የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት፣ 43 ሺህ 640 መኖሪያ ቤቶች እና ከ80 በላይ የመንግስት ተሸከርካሪዎች መውደማቸው ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የተፈናቃዮች ድርጅት ልዑካን በበኩላቸው ÷ተቋሙ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ሥራ የሚደግፍ ፕሮጀክት የመተግበር ፍላጎት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የመጠለያና የሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ በህብረተሰቡ ዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ድርጅቱ በፕሮጀክቱ አተገባበር ዙሪያ በቀጣይ ከክልሉ መንግስት ጋር አስፈላጊ ዝግጅቶችን በማድረግ ወደሥራ እንደሚገባ መገለጹንም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.