ኢትዮጵያና ቻይና በኢኮኖሚና በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለመተባበር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር ተወያይተዋል።
ኒውዮርክ ውስጥ እየተካሄደ ባለው 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ደመቀ መኮንን እና ዋንግ ዪ በኢኮኖሚ እና በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ አቶ ደመቀ ለቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በወቅታዊ ጉዳዮዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ቻይና በቀጠናው ሰላምና ልማት ዙሪያ የምታደርገውን አስተዋፅኦ አድንቀው÷ ቻይና በፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን አውስተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ አብራርተዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ቻይና የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ ነው ያረጋገጡት፡፡
የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በዓለም አቀፍ መድረኮች የፖለቲካ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ዋንግ ዩ÷ በሰብዓዊ መብት ስም የሚደረግን ጣልቃ ገብነት ቻይና በፅኑ ታወግዛለች ብለዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ እና በሰብዓዊ መስኮችም ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡