ሰላምን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሰላምን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ጉባዔ ላይ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው÷ሰላምን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ጠላት ህዝባዊና የሃይማኖት በዓላትን ለማወክ ዝግጅት ቢያደርግም መዋቅራችንን፣ መላ ህዝባችንን፣ የፀጥታ ሃይሉንና የተለያዩ አደረጃጀቶችን አቀናጅተን በመምራት የጠላትን እቅድ ማክሸፍ ችለናል ብለዋል፡፡
1 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ አካባቢውን እንዲጠብቅ በማደራጀት የሰላም ሰራዊቱ፣ የደንብ ማስከበር፣ የፖሊስ ሃይልን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ማስፈን እንደተቻለ መግለጻቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሀገር ሉዓላዊነትና ግዛት አንድነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የደጀንነት ስራን በማጠናከር ለሶስተኛ ዙር 486 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገምት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ እና አጎራባች የኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ህገ-መንግስቱንና የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ በጋራ በተቋቋሙ ኮሚቴዎች እና በፌዴራል መንግስት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እልባት በመስጠት ታሪካዊና ውጤታማ ስራ መስራት እንደተቻለም አንስተዋል፡፡