“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዓይን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ነው፡፡
የእንግሊዙ ዴይሊ ሜል ባወጣው ዘገባ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አደባባይ በመውጣት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን አስነብቧል፡፡
ሰልፈኞቹ አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንድታከብር ድምፃቸውን ማሰማታቸውን እና አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ውስጥ ለተከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶች ተጠያቂ ነው የሚሉ መልዕክቶች መተላለፋቸውን አስፍሯል፡፡
ሰልፎቹ በሚቀጥለው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን የሰላም ውይይት ከመጀመሩ አስቀድሞ የተደረገ ስለመሆኑም ያነሳል ዴይሊ ሜል፡፡
ሌላኛው ዓለማቀፋዊ ሚዲያ አፍሪካ ኒውስ ባወጣው ዘገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ሰልፎች መደረጋቸውን ዘግቧል፡፡
ሰልፈኞቹ የፌዴራል መንግስት እርምጃን እንዲሚደግፉ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደሚቃወሙ መግለፃቸውንም አንስቷል፡፡
ተሳታፊዎቹ አሜሪካ ለህወሓት የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም የሚጠቁሙ መፈክሮችን በመያዝ ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ነበር ብሏል አፍሪካ ኒውስ በዘገባው፡፡
በተመሳሳይ ብሎምበርግ ባወጣው ዘገባ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በዛሬው ዕለት የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን አስነብቧል፡፡
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች በተካሄደው ሰልፍም የህወሓት መሪዎች በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂ ናቸው የሚሉ መልዕክቶች መተላለፋቸውን አትቷል፡፡