አቶ ደመቀ መኮንን በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ጉብኝት አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዛሬው ዕለት በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ጉብኝት አድገዋል፡፡
አቶ ደመቀ በጉብኝታቸው÷ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት፣ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች፣ የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ እንዲሁም በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም መስኮች ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት በአምባሳደር አክሊሉ ከበደ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በዱባይና ሰሜን ኢሚሬቶች ከኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማኅበር እንዲሁም አቡዳቢ ከሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና ኮሚዩኒቲ ማኅበር እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተሳሰር እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱና ኮሚዩኒቲ ማኅበሩ በጋራ በመቀናጀት የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እያደረጉት ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ባለው ውስን ሐብት ብቻ የዜጎችን ችግሮች መፍታት የማይችል በመሆኑ ሁሉም የዳያስፖራ አባላትና አደረጃጀቶች የዜጎችን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ዙሪያ የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ እና የኮሚዩኒቲ ማኀበሩ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዱባይና ሰሜን ኢሚሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት በፈረንጆቹ 2004 የተከፈተ ሲሆን፣ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማጠናከር ጎን ለጎን በተለይ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የዜጎችን መብትና ጥቅም የማስጠበቅ፣ የዳያስፖራን ተሳትፎ የማሳደግ እና የሀገራችንን የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ማስፋፋት እንዲሁም የገጽታ ግንባታና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!