በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ድርጊት በፈጸሙ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ድርጊት በፈጸሙ የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በሰጡት መግለጫ፥ እርምጃው የተወሰደው በ121 ወረዳዎች በሚገኙ 206 ትምህርት ቤቶች ዙሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አዋኪ ድርጊቶችን በፈፀሙ 194 ጫት ቤቶች፣ 176 አረቄ ቤቶች፣ 21 ሕገወጥ ጋራዥ ቤቶች፣ 126 የላስቲክ ቤቶች ፣ 25 የሺሻ ቤቶች እንዲሁም 244 ሌሎች የንግድ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።
ከእነዚህ ንግድ ቤቶች መካከል 99 ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጉንም ነው ኃላፊዋ የገለጹት።
እርምጃ የተወሰደባቸው የንግድ ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ የሱስ ተገዢ የሚያደርጓቸው በመሆኑ እርምጃው ቀጣይነት ይኖረዋል ማለታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።