Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የት/ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል “ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡

መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ÷ትምህርት ከሌላው ዓለም ጋር የምንወዳደርበት ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ የትምህርት መሠረተ ልማት ግንባታዎችና ማሻሻያዎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ግብ መሣካትም የትውልድ ማበልጸጊያ የሆኑትን ትምህርት ቤቶች በመደገፍ ሁሉም ማህበረሠብ እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ የሠውዘር በላይነህ በበኩላቸው÷ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በመንግስት አቅም ብቻ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ አንስተዋል፡፡

ስለሆነም ማህበረሠቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት የሚሣተፋበትን ስርዓት ዘርግቶ መንቀሳቀስ ታምኖበት ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱሃሠን ያዬ ÷ በትምህርት ለትውልድ ህዝባዊ ንቅናቄ ከደረጃ በታች የሆኑ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል እቅድ ተይዞ ወደ ስራ እንደተገባ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.