የቻይና የህክምና ቡድን በምስራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ለሚሰሩ ሰራተኞች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና የህክምና ቡድን በምስራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ለሚሰሩ ሰራተኞች ነጻ የምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
“የኢትዮጵያ ሰራተኞችን ጤና እንጠብቃለብን” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው ነፃ ሕክምና በቻይና እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
በኢንዱስትሪ ዞኑ ለዛሬ ብቻ የተሰጠው ነፃ የሕክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ እና በቻይና የሕክምና ቡድን እንዲሁም ሌሎችም በጋራ ያዘጋጁት ነው ተብሏል፡፡
በነፃ ምርመራና ሕክምናው 30 ቻይናውያን ዶክተሮች በኢንዱስትሪ ዞኑ የሚሰሩ ከ350 በላይ ሰራተኞችን የመረመሩ ሲሆን ÷ ከእነዚህ መካከል 200 ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እና 150 ቻይናውያን ሰራተኞች ናቸው።
የሕክምና አገልግሎቱ የውስጥ ሕክምና፣ አጠቃላይ የቀዶ ሕክምና፣ የጥርስ ሕክምና፣ የጽንስና የማህፀን ሕክምና፣ የነርቭ ቀዶ ሕክምና፣ የአጥንት ህክምና፣ የዓይን ሕክምናና ሌሎችም ተካተውበታል።
ይህ ነፃ የህክምና አገልግሎት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን በማጠናከር እየተሰሩ ካሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መካከል መሆኑም ተመላክቷል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ