ሳዑዲ በባቡር መሰረተ ልማትና በአየር ትራንስፖርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት እንደምትፈልግ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ አረቢያ በባቡር መሰረተ ልማት እና በአየር ትራንስፖርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የኢትዮ-ሳውዲ ኢንቨስትመንትና ንግድ ፎረም ላይ በተሳተፉበት ወቅት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን በተመለከተ ለሳዑዲ አረቢያ የትራንስፖርት ሃላፊዎችና ባለሃብቶች ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዘርፉ ሥድስት ስትራቴጂክ የኢንቨስትመንት እድሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የሎጂስቲክስ ከተማ ማስፋፊያ፣ የባቡር ማስፋፊያ፣ የአቪዬሽን አገልግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የወደብ ማስፋፊያ መሰረተ ልማቶች ለኢንቨስተሮች ክፍት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከባቡር መሰረተ ልማት አንጻር አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የጭነትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ቢሆንም ከሀገሪቱ እድገት ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የባቡር መሰረተ ልማት እና የባቡር መለዋወጫ እቃዎች ለማምረት የኢንቨስትመንት እድል መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ከአቪዬሽን አገልግሎት ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ እስከ 25 ቶን ድረስ የጭነት ትራንስፖርት አቅም መኖሩንና የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለኢንቬስትመንት ክፍት መሆናቸውንም ጠቁመዋል አቶ ዴንጌ፡፡
በተለይ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከማዘመንና ከማስፋፋት አንጻር ሰፊ ክፍተት በመኖሩ በከተማ ውስጥና በሀገር አቋራጭ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የገመድ ትራንስፖርት እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት ስላለ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ትርፋማ መሆን እንደሚችሉም አረጋግጠዋል፡፡
የሳዑዲ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲከስ ዘርፍ ልዑክ እና የትራንስፖርት ድርጅት ባለሃብቶች በበኩላቸው፥ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለው የኢንቨስትመንት እድል ትልቅ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በባቡር መሰረተ ልማትና በአየር ትራንስፖርት ላይ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ማንሳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡