Fana: At a Speed of Life!

በጦር መሳሪያ ዝውውርና ቁጥጥር ላይ የሚወያይ የባለድርሻ አካላት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በጦር መሳሪያ ዝውውርና ቁጥጥር ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ፥ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት ኮሚሽነር ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች፣ ከክልል የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ከሚኒስቴሮች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፥ በጦር መሣሪያ አያያዝ፣ ቁጥጥርና ምዝገባ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት ማድረግ ስለሚገባ መድረኩ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸው፤ በዚህ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት ከፍተኛ የሴኩሪቲ ባለሙያ ኤሪክ ካይራኛ፥ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ ለሕገ-ወጦች ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ በመሆኑ የእነዚህን ግለሰቦችና ቡድኖች እንቅስቃሴ ለመግታት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የጦር መሣሪያ አያያዝና አመዘጋገብ እንዲሁም የጦር መሣሪያ አቀማመጥና አወጋገድ ላይ የፀጥታ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ በሀገር ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባም ማንሳታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጦር መሣሪያ ፍቃድና ጥበቃ ተቋማት ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዘካሪያስ ይርጋለም በበኩላቸው፥ መድረኩ በጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ግንዛቤና እውቀት የሚገኝበት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

እንዲወገዱ በጥናት ተለይተው የተሰበሰቡ የጦር መሳሪያዎች ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች፣ መኮንኖች፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች እና የሚዲያ ባለሞያዎች በተገኙበት በነገው ዕለት በኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ እንደሚወገዱም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.