የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባኤ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባኤ ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የምልዓተ – ጉባኤውን መጠናቀቅ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉና ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸው እንዲሁም በጥብቅ የሚያወግዛቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያንና ለሀገራችን ህዝቦች ጠቃሚ ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ አባታዊ ምክርና ተግሣጽ ማስተላለፍ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን አንስተው ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉና ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸው እንዲሁም በጥብቅ የሚያወግዛቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ወደ ፊት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉበኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑንም ጠቁመዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ሀሳቦችን ለሚመለከተው የመንግስት ተቋም መላኩን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊትም የተሰጡ የማሻሻያ ሐሳቦች በአዋጁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟልም ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ለአፈጻጸም እንዲያመችም የተዘጋጀው መዋቅራዊ አደረጃጀት በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውልም ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡