Fana: At a Speed of Life!

ለ10 ሺህ ወጣቶች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የክኅሎት ስልጠና ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ10 ሺህ ወጣቶች በስድስት ዩኒቨርሲዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ የክኅሎት ስልጠና የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ፡፡

መርሐ-ግብሩ የሚከናወነው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ)፣ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በሱሚቶም እና ገበያ ቴክኖሎጂ ተቋም ትብብር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በቅንጅት በመሥራት በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ወጣቶች ሥራ የሚፈጥሩበትን ክኅሎት መስጠትና ምቹ ስነ-ምኅዳር እንዲኖር ማድረጉ ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር ማሳሂሮ ሚያሺታ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ መሳካት አስተዋፅኦ ለማድረግ እና ፈጠራን በማስተዋወቅ የሕብረተሰቡን ተግዳሮቶች የሚፈቱ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ያለንን ቁርጠኛነት ለማሳካት ትብብሩ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የጃይካ ተወካይ ቺ ሺሞዳይራ በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ዲጂታል ክኅሎት አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት እና በዲጂታል መድረኮች ላይ ከሚገኙ አገልግሎቶች ጥቅም ለማግኘት ቁልፍ ሚና አለው ብሎ እንደሚያምን ጠቁመው÷ ለዚህም በትብብር ይሠራል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የገበያ ቴክኖሎጂ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አማዱ ዳፌ በክላውድ ታለንት አብዮት የቴክኖሎጂ አማራጭ፣ መፍትሄዎችና ገበያዎችን በመፍጠር የአፍሪካን እምቅ አቅም እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለመጨመር እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ÷ በዚህ ትብብር ይህንን ለማሳካት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ይህን የመጀመርያ ዙር ፕሮግራም ለማሳካት እንደ ማዕከል የሆኑት መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ እና ጂግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.