በኦሮሚያ ክልል የቡና ችግኝ ተከላ ሥራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች የቡና ችግኝ ተከላ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷የኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትን ጥራትና ብዛት በመጨመር የውጭ ምንዛሬንና የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከኦሮሚያ ዞኖች በብዛትና በጥራት ቡናን የማምረት ዓላማን በማሳካት ላይ ከሚገኙት ውስጥ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ አንስተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም እንደ ክልል ከተዘጋጀው 2 ነጥብ 6 ቢሊየን የቡና ችግኝ ውስጥ ከ120 ሚሊየን የሚልቀው በሁለቱ ጉጂ ዞኖች መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይም በጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች የቡና ችግኝ ተከላ ሥራ መጀመሩን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡
ያለውን ሰፊ እድል በመጠቀም የቡና ልማት በማስፋፋት ረገድ ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ቢታይም ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀም እጅግ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አሳስበዋል፡፡
የቡና ኢኒሼቲቭን ያስተዋወቀው የ”ነቀምቴ አዋጅ” በ2011 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ ወዲህ የተያዘውን ዓመት ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ቢሊየን የቡና ችግኝ በመልማት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ለቡና ምርት ጥራትና ብዛት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሀገራችንና አርሶ አደሮች ከአረንጓዴው ወርቅ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ይበልጥ የምናረጋግጥ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።