ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራት የስፖርት ሚኒስትሮች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የ2024 ዓለም አቀፍ ሩሲያ የብሪክስ ሀገራት የስፖርት ሚኒስትሮች ጠቅላላ ጉባኤ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡
በሩሲያ ካዛን ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደው በሚገኘው መድረክ ኢትዮጵያን በመወከል በመድረኩ የተሳተፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ናቸው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራት ማዕቀፍ የስብሰባ ሙሉ አባል በመሆኗ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የአባል ሀገራቱ ትብብር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ በኢትዮጵያ መንግስትና በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስም ልዩ ምስጋናና አቅርበዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ የስፖርት ልማትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነትና ትብብር ለማጠናከር የላቀ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ባለ ዘርፈ ብዙና ሀገር በቀል የሆኑ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማበረታታት ለዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድደር እንዲበቁ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ምክክር ተደርጓል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከሩሲያ ፌደሬሽን ስፖርት ሚኒስትር ሚካኤላ ደገተያሪቨ ጋር በስፖርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረው ከስምምነት መድረሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።