ም/ቤቶች የዜጎችን ዕኩል ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባቸው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክር ቤቶች የዜጎችን መብትና ዕኩል ተጠቃሚነት የማረጋገጥ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን የመቆጣጠር ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ተመላከተ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየዓመቱ የሚካሄደው የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ “የኢትዮጵያ ፓርላማ ለሕዝብ ጥቅምና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ” በሚል መሪ ሐሳብ ለ4ኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ምክር ቤቶች የሕዝብ ውክልናና ሉዓላዊነት የሚረጋገጥባቸው የዲሞክራሲ ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዜጎችን መብትና ዕኩል ተጠቃሚነት የማረጋገጥ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን የመቆጣጠር ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ኮንፈረንሱ ምክር ቤቶች ሥራቸውን በጥናትና ምርምር የተደገፈና ሣይንሳዊ መንገድን የተከተሉ መፍትሔዎችን ለማቅረብ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እስከ አሁን የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና 4ኛው ኮንፈረንስ ጠቃሚና ገንቢ ሐሳቦች የሚገኙበት እንደሚሆን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ በአራቱ የምክር ቤቱ ዋና ዋና ተልዕኮዎች በሕግ አወጣጥ፣ በሕዝብ ውክልና፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ 10 የምርምርና ጥናት ሥራዎች እንደሚቀርቡ ተመላክቷል፡፡