Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተጠናቀቀው ዓመት 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ቡና መሰብሰቡን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 የምርት ዘመን 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የቡና ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኦሮሚያ ክልል ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ስራ ባስገባቸው ኢኒሼቲቮች ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ዓይነትና ጥራት የሚጨምሩ ኢንሼቲቮች ወደ ሥራ ካስገባ ወዲህ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እና ከውጪ የሚገኘው ምንዛሬ አድጓል ነው ያሉት፡፡

ከኢንሼቲቮቹ መካከልም÷ የቡና፣ የአቮካዶ፣ የሻይ ቅጠልና የሙዝ ልማት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም ከ2011 ዓ.ም የነቀምት የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ አዋጅ በኋላ በቡና ምርት ብዛትና ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ክልል በ2015 ዓ.ም 1 ነጥብ 33 ቢሊየን የቡና ችግኝ መተከሉን አስታውሰው÷ በዚህ ዓመትም ለተከላ ከተዘጋጀው 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኝ እስከ አሁን 2 ነጥብ 1 ቢሊየኑ መተከሉን አረጋግጠዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም የምርት ዘመንም 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የቡና ምርት መሰብሰቡን ነው ያስታወቁት፡፡

እንደ ሀገር ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ለተገኘው 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢም፤ ባለፉት አምስት አመታት በክልሉ የተከናወኑ የቡና ልማቶች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም በዚህ ዓመት እንዲተከል ከተዘጋጀው 17 ሚሊየን ምርጥ ዘር የአቮካዶ ችግች እስከ ዛሬ ድረስ ከ7 ሚሊየን በላይ ተተክሏል ብለዋል፡፡

ከ”አደዓ ዲክላሬሽን” ወዲህ ባሉት አምስት ዓመታት ባከናወንናቸው ሥራዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውን ምርጥ ዘር የአቮካዶ ዝርያ በ16 ሺህ ሄክታር አልምተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ክረምት በ25 ሺህ ሄክታር ላይ ለማልማት የያዝነውን ዕቅድ በመተግበር÷ አጠቃላይ የኤክስፖርት አቮካዶ ዝርያ ሽፋናችንን ከ41 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የምናሳድግ ይሆናል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በአሌ የሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቫችን ከፍተኛ የምርት ጥራትና እድገት አስመዝግበናል ያሉት አቶ ሽመልስ÷ በዚህ ዓመትም በብዙ እጥፍ ለማሳደግ እየሠራን ነው፤ በዓመቱ 413 ሚሊየን ችግኝ ተዘጋጅቶ በ30 ሺህ ሄክታር ላይ የማልማት ስራም ጀምረናል ብለዋል፡፡

ከሻይ ቅጠል ምርት እንደ ሀገር ለተገኘው 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሪም÷ ከአሌ አዋጅ በኋላ የተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

ሌላው ውጤት እያስገኘ ያለው ኢኒሼቲቭ የሙዝ ልማት (የኢሉ ገላን ዲክላሬሽን 2011 ዓ.ም) መሆኑን በማመላከት በዚህ ኢኒሼቲቭ በውድ የውጭ ምንዛሬ ከውጪ ይገባ የነበረውን ምርጥ ዘር የሙዝ ችግኝ በግብርና ምርምር ተቋሞቻችን በማልማት ማስቀረት ተችሏል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም እስከ 2015 ዓ.ም በቲሹ ካልቸር የተዘጋጀ የሙዝ ምርጥ ዘር በ3 ሺህ ሄክታር ላይ በክላስተር ማልማት ችለናል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ዓመትም የእስከ አሁኑን ሽፋን ከሦስት እጥፍ በላይ በማሳደግ 10 ሺህ ሄክታር ላይ 17 ሚሊየን የሙዝ ምርጥ ዘር ችግኝ መተከሉን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የሙዝ ምርጥ ዘር ሽፋናችንን 13 ሺህ ሄክታር እንዲሁም አጠቃላይ የሙዝ ሽፋናችን 37 ሺህ ሄክታር አድርሰናል ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሲቀርብ የነበረውን የሙዝ ምርትም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡

እነዚህ ኢኒሼቲቮች የሀገር ውስጡን ገበያ ከማረጋጋት አልፈው ለዓለም አቀፉ ገበያ በሚያቀርቡ አርሶ አደሮቻችን እና በሀገር አቀፉ ኢኮኖሚ ላይ ጥሩ መነቃቃት በመፍጠር ላይ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የግብርና ምርታችንን የዓለም አቀፉን ገበያ ታሳቢ በማድረግ የምናለማ ይሆናል ሲሉም አመላክተዋል፡፡

የእስከ አሁኑ ስኬት የተገኘው በአርሶ አደሮች ትጋት መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ምስጋና በማቅረብ÷ የቤተሰብና ሀገራዊ ብልጽግና ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋገጥ መንግሥት በሁሉም መስክ ከአርሶ አደሩ ጎን መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.