ኮሚሽኑ ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር በተደረገው ሥራ ውጤት አስመዝግቧል- አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር በተደረገው ሥራ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ሲካሄድ የነበረው የ2016 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ 6ኛው የጋራ ምክክር መድረክ ተጠናቅቋል፡፡
በመድረኩም የ2016 በጀት ዓመት የክልል፣ ከተማ አስተዳደርና የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ኮሚሽን ሪፖርት እና የኮሚሽኑ የተጠቃለለ የግምገማ ሪፖርት እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት መሪ እቅድ ቀርቧል፡፡
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊት ከክልል፣ ከተማና ፌዴራል ተቋማት ኮሚሽን ሰብሳቢዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በ2016 በጀት ዓመት የፓርቲው የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ውጤታማ መሆኑን በማንሳት÷ ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ያስቻሉ ሶስት ምክንያቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
አንደኛው ጠንካራ የፓርቲ መዋቅር መፍጠር እንደሚገባን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ተግባር በመገባቱ ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በየደረጃው የሚገኘው የኮሚሽኑ መላው አባላትና አመራር ተንቀሳቅሶ መስራቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሶስተኛው ኮሚሽኑ ተልዕኮውን መወጣት እንዲችል “3ቱ መ’ዎች ማመን፣ መደገፍና መተግበር” በሚል መርህ ወደ ስራ መግባታችን ነው ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ “ጠንካራ ኢንስፔክሽን ፤ ለጠንካራ ፓርቲ” በሚል በጀመረው ንቅናቄ የፓርቲው የፖለቲካ ጥራት እንዲረጋገጥ፣ ሥነ-ምግባር እንዲሻሻል፣ አሰራሮች እንዲጠበቁ፣ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ እንዲሁም በፓርቲው በሀብትና ንብረት ላይ የሚደረገው ኢንስፔክሽን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።