Fana: At a Speed of Life!

ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎች የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ34 ሀገራት የተውጣጡ የቅድመ ታሪክ ተመራማሪዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።

ከ230 በላይ የሚሆኑት ተመራማሪዎች ሉሲ የተገኘችበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለመሳተፍ የመጡ ናቸው፡፡

ተመራማሪዎቹ በዛሬው ዕለት የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ብሄራዊ ሙዚየምና አንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።

ጎብኝዎች በጎበኟቸው ስፍራዎች የኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ባለቤትነቷን ማየታቸውን በመግለጽ ታሪካዊ ቅርሶችን መንከባከብና ለትውልድ ማስረከብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥብቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ የ13 ድንቅ ግኝቶች ባለቤት መሆኗን በመጥቀስ ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ያላትን እንዲያውቁ የሚረዳ ነው ብለዋል።

የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት (የወርቅ ኢዮቤልዩ) የኢትዮጵያን ምድረቀደምትነት እና አሁን የተሰሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለዓለም ማስተዋወቅ በሚያስችል መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.