በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ሙሉ መልዕክት
ለመላው የክልላችን ህዝቦች፤ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊን፤ እንኳን ለ2017 ዓ.ም አዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ አዲሱ አመት የሰላም፤የደስታ እና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን የራስዋ የዘመን አቆጣጠር ፍልስፈና ያላት ሀገር መሆንዋ ልዪ ያደርጋታል። በሁሉም የአለም ሀገራት አሮጌዉ አመትን ሸኝተዉ አዲስ አመት ሲቀበሉ የመልካም ምኞት መልዕክት መለዋወጥ እና አዲስ ተስፋን ሰንቆ በአዲስ ራዕይ ለሌላኛዉ የህይወት ጉዞ ዉጥን ማበጀት የተለመደ ነዉ።
የኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አመትን ለየት የሚያደርገዉ ግን የራሱ የዘመን መለወጫዉ ይዞት የሚመጣዉ አዳዲስ ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶች አሰደሳች እና ተስፋ ሰጪ፣ ለአዲስ የህይወት መንገድ አዲስ ራዕይ የምሰንቅበት መሆኑ ነዉ። የዘመን መለወጫን የምናከብረዉ መለያችን የሆነዉ አደይ አበባ በየጋራዉ እና ሸንተረሩ ፈክቶ አዲስ ገፀበረከት ይዞ እየመጣ መሆኑን ሲያበሰር፣ አስፈሪዉ እና ነጎደጓዳማዉ የክረምት ወራት አልፎ በጉም የተሸበበችዉ የተስፋ ተምሳሌት ፀሐይ ፈገግ ሰትል፣ ዘመድን ከዘመድ የላያየዉ አሰፈሪዉ የከረምት ጅረት ጎሎ ዘመድን ከዘመድ ማሻገር ሲጀመር፣ ክረምቱን የተደከመበት አዝመራ አብቦ በደረስኩለህ የተስፋ መልዕክት አርሶ አደሩን በሚቀበልበት፤ መምህራን ለትዉልድ ግንባታ ተማሪዉ ለእዉቀት ሸመታ በሚሰናዱበት መሆኑ የእዉነት የኛን የዘመን ሽግግር አስደሳች እና ተስፋ የሚያሰንቅበት ያደርገዋል።
ዘመን ለዘመን ቦታዉን ሲለቅ ያለፈዉ ትዉስታ ሆኖ ትምህርት ሲወሰድበት አዲሱ ደግም ራዕይ የሚሰነቅበት ይሆናል። ከዚህ አንፃር ባገባደድነዉ 2016 ዓ.ም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልላቸን በርካታ ድሎችና ተግዳሮቶችን አስተናግደናል። በሁለም ዘርፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለወጠነዉ ራዕይ ስኬት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል። በተለይም እንደ ክልላችንም ሆነ እንደ ሀገር በዙርያችን ያሉትን የመልማት እድሎችን እና ገፀ በረከቶችን አሟጠን በመጠቀም ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገር አለብን ብለን የለኮስነዉ የቁጭት ንቅናቄ በግብርናዉ ዘርፍ በተለይም ደግም በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገብን ሲሆን፤ በአገልግሎት፣ በእንዱስትሪ ፤ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፍም በርካታ ደሎችን መጎናፀፍ ችለናል፡፡
2016 በርካታ ድሎችን ያስመዘገብንበት ቢሆንም ፣ ነጠላ ትርክት ወለዶ ያሳደገዉ ፅንፈኝነት የሰላማችን ዋንኛ ተግዳሮት በመሆን ህዝባችንን ዋጋ አስከፍሏል። ፅንፈኝነት ለግዜው እርምጃችንን ቢገዳደረም ህዝባዊ መሠረት ስለሌለዉ በሂደት እንደ ጉም በኖ በመጥፋት የህዝባችን አንድነት እና ሀገረ መንግስታችን በብሔራዊ አርበኝነት ትርክት ፅኑ መሠረት ላይ ይገነባል። ይህ ይሆን ዘንድ፤ አኛ ኢትዮጵያዊያን እጣ ፈንታችን ላይለያይ የተጋመደ መሆኑን በውል በመረዳት በአዲሱ ዓመት የጀመርነዉን የብሔራዊ አርበኝነት ትርክት ግንባታ ፅኑ መሠረት ላይ በመትከል ሠላማችን እና ሁለንተናዊ በልፅግናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በጋራ የምንቆምበት መሆን አለበት።
በመጨረሻም፣ ለመላዉ የክልላችን እና የሀገራችን ህዝቦች፤ በተለይም ደግም ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ እና ክብሯ የተጠበቀን ሀገራችሁን ለትዉለድ ለማስተላለፍ በዚህ ሰዓት ዝናብ፣ ብርድ እና ፀሐይ ሳትሉ ለውዲቷ ሀገራችሁ ሰላም እና ልማት ዘብ ለቆማችሁ መላዉ የፀጥታ አካላት እንኳን ለ2017 ዓ.ም አዲስ አመት በሠላም አደረሳችሁ እያልኩ አዲሱ ዘመን ሠላማችን አሰተማማኝ የሚሆንበት፣ የሁለንተናዊ ብልፅግና ጉዟችን እምርታ የሚመዘገብበት፣ ሁሉም በተሠማራበት ስኬት የሚያስመዘግብበት በአጠቃላይ በአዲስ የራዕይ ስንቅ ለተሻለ የስኬት ጉዞ የምንዘጋጅብት አንዲሆንልን ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡