Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከካርበን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ያሳድጋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በየአመቱ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ነው አለ የኢትዮጵያ የደን ልማት።

በተቋሙ የካርበን ልቀት ቅነሳ ፕሮግራም ብሄራዊ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደተናገሩት፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሁን ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን በመጨመር የካርበን ሽያጭን ለማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግና በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መልኩ የካርበን ሽያጭ ለማከናወን እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁንም እንደ ሃገር ከካርበን ሽያጭ ከ500 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንና አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

የካርበን ሽያጭ የደን መጨፍጨፍን በመከላከል ለተጠበቀው ደን ወይም አዳዲስ ችግኞችን በመትከል የካርበን ልቀትን በመቀነስ ደን ላበረከተው አስተዋጽኦ የሚከፈል ክፍያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ክፍያው ደን ለአካባቢውና ለአየር ንብረት ሚዛናዊነት ጥበቃ በያዘው የካርበን መጠን በቶን ተለክቶ ያደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚከፍሉት የገንዘብ ክፍያ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በተለይም ደኑ ምን ያህል ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን እንዲሁም የደኑ ሁኔታ፣ የካርበን መያዝ አቅሙና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች በዲጂታል መልኩ በጂ ፒ ኤስ ተመዝግበው መቅረብ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.