ለጋምቤላ ክልል መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለጋምቤላ ክልል የትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የክልሉ የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር የይ ቾል ሆስ እንዳሉት ÷ የክልሉ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በጅማና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየወሰዱ ነው፡፡
መምህራኑ በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት እና ክህሎት ዘርፍ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ በላይ መምህራንን ለማሰልጠን ታቅዶ እንደነበር ጠቁመው÷ በተለያዩ ምክንያቶች 836 ያህሉን ብቻ የስልጠናው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ስልጠናው መምህራን የማስተማር አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት በመሆኑ የመማር ማስተማር ሒደቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም መምህራን ብቁ ሆነው በተገቢው መንገድ ዕውቀታቸውን ለተማሪዎቻቸው ማስተላለፍ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥር ነው ያስገነዘቡት፡፡
በሶስና አለማየሁ