Fana: At a Speed of Life!

የበካይ ጋዝ ቁጥጥር መመሪያ በቀጣይ 2 ወራት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል አለ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር።

በሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ አዲስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ለመተግበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ስለሆነም ተሽከርካሪዎችን ለምርመራው ዝግጁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ተሽከርካሪዎች የተቀመጠውን የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ደረጃ የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ተሽከርካሪዎች የተቀመጠውን ደረጃ ለማሟላት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ተሽከርካሪዎች ፈቃድ በተሰጣቸው መመርመሪያ ተቋማት ለማስመርመር እና ቴክኖሎጂዎችን ለማስገጠም መዘጋጀት እንደሚገባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አሁን ላይ ፈቃድ ያላቸውና አስፈላጊው ምርመራና ፍተሻ እየተደረገባቸው የሚገኙ የበካይ ጋዝ ልቀትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ የመኪናዎችን ዕድሜ የሚገድብ መመሪያ አለማውጣቱን የተናገሩት አማካሪው ÷ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ዓመታዊ የምርመራ ደረጃውን በማሟላት አገልግሎቱን መቀጠል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.