በመዲናዋ ለ976 ሺህ 702 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በ2018 ትምህርት ዘመን ለ976 ሺህ 702 ተማሪዎች የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል አለ የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጄንሲ፡፡
የኤጄንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢ ሁኔታ እንዲከታተሉ እያደረገ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የተማሪዎችን ት/ቤት የመቅረት ምጣኔ ከመቀነስ ባለፈ ለአዕምሯዊና አካላዊ እድገታቸው አዎንታዊ ሚና አንዳለው አስረድተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለሚገኙ 840 ሺህ 585 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመትም ከ10 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ ለ976 ሺህ 702 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ተድርጓል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል በማሕበረሰብ አቀፍ ምገባ በ26 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ለ36 ሺህ 600 ዜጎች አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጨማሪ 6 ማዕከላትን በመገንባት እስከ 41 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን የተስፋ ብርሃን ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተማሪዎችና በተስፋ ብርሃን ምገባ አገልግሎትም ለ16 ሺህ እናቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ነው ም/ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!