ሩሲያ፣ ኢራን እና ቻይና የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ሊያካሂዱ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍቢሲ) ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና የአለም አቀፉን ንግድ ደህንነት ማስጠበቀ የሚያስችል የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ሊያደርጉ ነው።
ሀገራቱ ከፊታችን ዓርብ ዕለት ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ሊያካሂዱ መሆኑን የኢራን ጦር ሃይል ቃል አቀባይ አስታውቋል።
የጋራ የባህር ሃይል ልምምዱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ የንግድ መስመር በሆኑት በሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ እና ኦማን ባህር ላይ የሚካሄድ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የጋራ የባህር ሃይል ልምምዱ በቀጠናው የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን የኢራን ጦር ሃይል ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል አቦልፋዝዮ ሺካሺ ተናግረዋል።
በተለይም በህንድ ውቅያኖስ እና ኦማን ባህር ላይ የሚስተዋለውን የባህር ላይ ውንብድና እንዲሁም የሽብር እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስወገድ ያስችላል ነው ያሉት።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ሀገራቸው ከቻይ እና ኢራን ጋር የጋራ የባህር ሃይል ልምምድ ልታደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለዚህም ሩሲያ ተገቢ ዝግጅት ማድረጓን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
በሌላ በኩል የጋራ የባህር ሃይል ልምምዱ የሀገራቱን ወታደራዊ ግንኙነት ከማጠናከሩ በሻገር ሞስኮ እና ቤጂንግ ለቴህራን ያላቸውን ድጋፍ የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።