የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ባለመው ኮንፈረንስ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ህዝቦችን ግንኙነት በሠላምና በልማት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አቋቁመው የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ናቸው።
በኮንፈረንሱ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ገመዳ ፈቃዱ፥ “እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ፌዴራሊዝም ስርዓት ተመራጭ ነው” ብለዋል።
በፌዴራሊዝም ስርዓት ውስጥ ስምምነት፣ መቻቻል፣ መተባበር፣ መተዋወቅን ማዳበር፣ ተጠያቂነትን መውሰድና ሥራዎችን በጥንቃቄ መፈጸም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ሁሉንም ያቀፈ የልማት ተጠቃሚነትን እና ፍትህን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመለየት ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን የሁለቱን ክልል ህዝቦች ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
“በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው አለመግባባት በፖለቲከኞች የመጣ ነው” ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ የሁለቱን ህዝቦች በሠላምና በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመው የጋራ ጽህፈት ቤት የጀመራቸው ተግባራት እንዲጠናከሩም ጠይቀዋል።
የሚፈጠሩ ግጭቶችን አላስፈላጊ መልክ እንዲይዙ ለማድረግ የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም የጠቀሱ ሲሆን፥ ግጭቶችን ሳይሰፉና ጉዳት ሳያደርሱ መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ህዝቦቹ በጋራ ሆነው ለሀገሪቱ ለውጥ ጥረት ማድረጋቸውን እንዲያጠናክሩም መጠየቃቸውንም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።