“ዐፄ ደመራ” በጎንደር
አዲስ አበባ፣መስከረም 17፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደርና በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አንዳንድ ከተሞች ደመራ የሚለኮሰው ዛሬ ነው።
በንግስት እሌኒ ዘመን አይሁዳውያን በጎልታ ተራራ የቀበሩትን የክርስቶስ መስቀል ደመራ ለኩሰው ያገኙበት ቀን መስከረም 17 ላይ ስለሆነ በጎንደርና አካባቢው ደመራ የሚለኮሰው በዚህ ቀን ነው።
በጎንደር መንበረ መንግስት መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ትርጓሜ መምህርና የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት፥ የክርስቶስ መስቀል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ከቆየበት በደመራ ጢስ ጥቆማ አማካይነት የተገኘበትን ቀን ለማሰብ የደመራ በዓል በዛሬው ዕለት ተከብሮ ይውላል።
የታሪክ ተመራማሪው እጩ ዶክተር ሲሳይ ሳህሌ እንደሚገልፁት÷ በነገሥታቱ የበዓል አከባበር ስርዓት የሚመራው የመስቀል አከባበር ልዩ ገፅታ አለው።
መስከረም 16 ዝግጅቱ የሚጀምረው የመስቀል በዓል አከባበር በንጉሡ አደባባይ “ጃንተከል ዋርካ” ወይም በፊት በር ነው።
ይህ ሥፍራ ከጥንት ጀምሮ የከተማዪቱ ዋና አደባባይ ሲሆን፥ በአጠገቡም ርዕሰ አድባራት አደባባይ፣ ኢየሱስ እና አደባባይ ተክለሃይማኖት ይገኛሉ።
ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ደማቁን ዓመታዊ የመስቀል በዓል ከማክበር ባሻገር አዋጅ የሚነገርበት፣ ሹምሽር የሚለፈፍበት፣ ደጅ የሚጸናበት እና ለመሳሰሉት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግባራት የሚያገለገል ሥፍራ ነበር።
በዚህ ሥፍራ የመስቀል በዓል አከባበር የሚጀምረው በዋዜማው ሲሆን፥ በተለይም ከሰዓት በኋላ በአርበ-ፀሐይ ከየአብያተክርስቲያናቱ የመጡ ካህናትና ሊቃውንት ጸሎት ይደርሳሉ።
ይህ ሥፍራ ከዋዜማው ጀምሮ ከየትኛውም ዓይነት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አገልግሎቶች ገሸሽ ብሎ ሃይማኖታዊውን ሥርዓት ብቻ ያስተናግዳል፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ÷ የመስቀል በዓል በጎንደር ሲታሰብ “ዐፄ ደመራ” አይዘነጋም።
“ዐፄ ደመራ” ማለት የንጉሠ ነገሥቱ ደመራ ማለት ሲሆን፥ የሚደመረውም በንጉሠ ነገሥቱ አደባባይ ላይ ነበር።
የንጉሠ ነገሥቱ ደመራ በዋናው አደባባይ ሲደመር የቀሩቱ በየአብያተ ክርስቲያናት፣ በየመንደሩና በየአባወራዎቹ መኖሪያዎች ይደመራሉ።
ዐፄ ደመራ የተባለበት ዋናው ምክንያት ከክብሩና ከሞገሱ የተነሳ ሲሆን፥ ከዚህም የተነሳ ይህ ደመራ የሚለኮሰው በየመንደሩ እና በየአብያተ ክርስቲያናቱ የተደመሩት ደመራዎች ከተለኮሱ በኋላ ነው።
በአብያተ መንግሥታቱ ግቢ ውስጥ፣ ዙሪያና አካባቢ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ካህናት ወደ ዐፄ ደመራ መሄድ የሚጀምሩት ጸሎተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።
ምናልባትም በዓሉ ረቡዕ ወይም ዐርብ ቀን የሆነ እንደሆነ፥ ጸሎተ ቅዳሴው የሚጀመረው ከእኩለ ቀን በኋላ ስለሆነ ማለዳ ቅዳሴ አይኖረም።
ይሁን እንጅ በየዓመቱ እንደሚደረገው፥ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ቀሳውስት እና ዲያቆናት የመፆር መስቀል በክብር አጅበው ይመጣሉ።
መዘምራኑም በዓሉን የተመለከተ በከበሮ ታጅበው መዝሙር እየዘመሩ እስከ አደባባዩ ይዘልቃሉ።
ከዚያም ሁሉም ማለትም ካህናቱ፣ መዘምራኑ፣ ሹማምንቱና ምዕመናኑ እንደየ ክብራቸውና ማዕረጋቸው ይቆማሉ።
ይህ ጥንት የነበረ አሁንም ያለ ባህል ሲሆን፥ የቀድሞውን ለየት የሚያደርገው የነገሥታቱ በክብረ በዓሉ ላይ መገኘት ነው።
መስከረም 16 ቀን ደመራውን በመደመር የሚጀመረው የበዓሉ አከባበር በየመንደሩ ባሉ ልጆች የሆያሆዬ ጭፈራ ይደምቃል።
ይህ ጭፈራ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ድረስይቀጥላል።
በዋዜማው የሰርክ ጸሎት የተባረከው ደመራ በማግስቱ ማለትም መስከረም 17 ቀን እኩለ ቀን ላይ እስኪቃጠል ድረስ በካህናቱና መዘምራኑ በኩል ያለው ጸሎትና በምዕመኑ በተለይም በወጣቱ ዘንድ የተለመደው ጭፈራ ይቀጥላል።
ሃይማኖታዊው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከጠናቀቀ በኋላ ደመራው ይለኮሳል፣ እልልታው ይቀልጣል፣ ጭፈራው ይደራል ።
በዚህ ወቅት አደባባዩ ለምእመኑ ይጠባል።
ከዚያም ደመራው ከወደቀ በኋላ በጸሎተ ቡራኬ በአደባባዩ የተካሄደው የበዓሉ አከባበር ፍጻሜ ይሆንና ማህበራዊው አከባበር ይቀጥላል።
እርሱም በየመንደሩ በዓሉን አስመልክቶ ግብዣ ይደረጋል፤ ማምሻውንም ዓመት ያድርሰን ተብሎ ስዕለት የመሳል ክፍሉ ይቀጥላል።
የጎንደር የመስቀል በዓል ልዩ ገፅታዎች፦
1. ከታሪካዊው የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና አብያተክርስቲያናት ግቢ ግርጌ የሚከበር መሆኑ፣
2. ለዘመናት የቀጠለው ዐፄ ደመራ ደማቅ አከባበር ሳይበረዝ፣ ሳይከለስና እና ሳይስተጎል መቀጠሉ እና
3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናኑ ከበዓሉ አከባበር በኋላ በየመንደሩ የሚያዘጋጁት ዝክር በከተማዋ ለሚከበረው የመስቀል በዓል ልዩ ገፅታን ይሰጣሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ በዓል በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
በዚህም ይህ ዓለም አቀፍ ክብርን የተጎናጸፈው ክብረ በዓል በተማሳሳይ መልኩ የዛሬ 35 ዓመታት አካባቢ በተመዘገበው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ግቢ ግርጌ መከበሩ የጎብኚዎችን ቀልብ እንዲስብ አግዞታል። ስለሆነም ሁለቱም ቅርሶች የኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ቅርስ ናቸው።
በነብዩ ዮሐንስ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!