ተማሪዎችና መምህራን በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ሲሳተፉ ውለዋል-ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአንድ ሳምንት መደበኛ ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዛሬው እለትም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን ሰብል በመሰብሰብ፣ ደም በመለገስ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ሲያከናውኑ መዋላቸውን ከሚኒስቴሩ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መዘጋቱን ተከትሎ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተው እየተከናወኑ ሲሆን እስከ አርብ ድረስ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተመላከተው፡፡
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን የሚሳተፉበት የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል የመሰብሰብ ዘመቻ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የትምህርት ቢሮው የዕቅድ ዝግጅትና የትምህርት ፕሮግራሞች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሒም÷ ይህ ተግባር መምህራንና ተማሪዎች የአገር ሉዓላዊነትንና አንድነትን ለማስከበር በየግንባሩ ለዘመቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በተለያዩ አካባቢዎች ፀጥታ ለማስከበር የተሰማሩ የሚሊሻ አባላትን ሰብል በመሰብሰብ ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹበት ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል በሐረሪ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የዘማች ቤተሰብ አርሶ አደሮችን ሰብል መሰብሰብ ጀምረዋል።
የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደተናገሩት÷ የክልሉ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ማህበረሰብ በሶፊ ወረዳ በመገኘት የዘማች ቤተሰቦችን የደረሱ ሰብሎች ሰብስበዋል፡፡
በተጨማሪም በጅማ ዞን የቀርሳ ወረዳ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ሚሊሻ ቤተሰቦችን እህል ሰብስበዋል፡፡
የወረዳው ተማሪዎችና መምህራን በቀጣይ ቀናትም የሌሎች ዘማች ቤተሰቦችን እህል እንደሚሰበስቡ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃምዛ መንግስቱ ተናግረዋል፡፡
በሙክታር ጣሃ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!