Fana: At a Speed of Life!

ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ እንስሳት ዝርያን ለማሻሻል ቁልፍ አቅጣጫ ይዘን እየሰራን ነው- ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ እንስሳት ዝርያን ለማሻሻል ቁልፍ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ድርቅ የፈተነው የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት በሚል ርዕስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የወተት ከብቶች እርባታ፣ የዶሮ ስራና የስጋ ስራ በእቅድ ተካቶና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በረዥምና አጭር የዝናብ ወቅቶች ላይ በተከሰተ የዝናብ እጥረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አጎራባች አገሮች ድርቅ ተከስቷልም ነው ያሉት፡፡

በሶስት ክልሎች በደቡብ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ አጠቃላይ በ19 ዞኖች፣ በወረዳ ደረጃ ደግሞ 92 ወረዳዎች ላይ ድርቁ እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡

ከ180 ሺህ በላይ አባዋራዎችና እማዎራዎች በድርቁ ምክንያት እየተቸገሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በቆላማው የኢትዮጵያ ክፍል ዋና የኑሮ መሰረት የሆነው እንስሳት እርባታ ነው ብለዋል፡፡
ድርቅ ሲከሰት በዋናነት የመኖና የውሃ እጥረት እንደሚከሰት ጠቅሰው፥ በዚህ ምክንያት ብዙ እንስሳቶች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለሚቀንስ በበሽታ የመጠቃትና የመሞት አጋጣሚዎች እንዳሉ አመላክተዋል፡፡

ከሁሉም ቦታዎች ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚደርሱ እንስሳቶች እንደሞቱና በዚህ ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጉዳት አብራርተዋል፡፡

ሁሉም አካላት ይሄንን ችግር የጋራ አድርገው በመረባረብ ሊደርስብን የሚችለውን ጉዳት መቋቋምና መቀነስ ይኖርብናልም ነው ያሉት፡፡

በግብርና ሚኒስቴር 110 ሺህ የሚሆን የመኖ ሳር እስር ለሶስቱም ክልሎች መከፋፈሉን ገልጸው÷ ከግለሰብ ጀምሮ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመኖ ሳር ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከሌሎች አካላት የተሰበሰበ 600 ሺህ የሚሆን የሳር እስር ተከፋፍሏል ብለዋል።

በሻምበል ምህረት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.