በክልሉ የቡና ምርትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በእጥፍ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ርዕሠ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሠ መስተዳድሩ ዛሬ በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን የቡና ማሳ በጎበኘበት ወቅት በዘርፉ እየተሰራ ስላለው ሥራ ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ያረጁ የቡና ዛፎች መጎንደላቸውንና 2 ነጥብ 9 ቢሊየን አዲስ የቡና ችግኞች መተከላቸውን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
የተተከሉት አዲስ የቡና ችግኞች የተሻለ ምርት ሊያስገኙ የሚችሉ ዝርያዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ ነባር 200 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን የጠቆሙት ርዕሠ መስተዳድሩ÷ ተጨማሪ 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አዲስ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው÷ ይህም በክልሉ የቡናን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
በሙክታር ጠሃ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!