Fana: At a Speed of Life!

ከውጭ የሚገቡ የግብርና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከውጭ የሚገቡ የግብርና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።

በአርሲ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ  በሃይሉ ዘነበና ደቹ ቱፋ እንደሚያስረዱት፥ ኢ-ሚዛናዊ የንግድ ስርአት እያደጉ ባሉ ሀገራት ፈጥነው ከድህነት እንዳይወጡ ትልቅ ተፅዕኖ የሚያደርግ ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ ምርትን በስፋትና በጥራት ማምረት እንዲሁም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ሃይሉ ዘነበ በበኩላቸው፥ ምርት የጀመሩ አምራች ኢንደስትሪዎችም ከውጭ ምርት ጫና ሊጠበቁ ይገባል ይላሉ።

የበርካታ ሀገራት ተሞክሮም በጅምር ያሉ አምራች ኢንደስትሪዎች  አቅማቸውን አጎልብተው ወደ ውጭ መላክ እስኪችሉ በመንግስት ሊደገፉ ይገባልም ብለዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች ልማትና ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አያሌው አባው በበኩላቸው፥ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ከምታገኘው ገንዘብ በበለጠ ወደ ሀገር ውስጥ በገቢ ንግዱ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ  ይናገራሉ።

ይህንን ለመቀነስ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ እና በትግራይ ክልሎች በግንባታ ሂደት ያሉ 4 አግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች ተስፋ መሆናቸውን ያነሳሉ።

ዳይሬክተሩ ጨምረውም  የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምሩ የሚነሱ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ከመቅረፍም በላይ ሀገሪቱ በአለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያግዛል ብለዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ፍጆታን በሀገር ውስጥ አምራቾች መሸፍን መቻል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም አሳስበዋል።

በማርታ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.