Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኡሞድ የጋምቤላ ክልል ሕዝብ የክረምቱን ወቅት ችግኝ በመትከል እንዲያሳልፍ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ሕዝብ እንደቀድሞው ሁሉ በክረምቱ ችግኝ በመትከል እንዲያሳልፍ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በጋምቤላ ወረዳ ኢሌይ ኢችዋይ ቀበሌ ተገኝተው ክልል አቀፍ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርን አስጀምረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም÷ አረንጓዴ ዐሻራን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በክልሉ ያለው የደን ሃብት እንዲያድግና የተመቸ ሥነ-ምኅዳር እንዲኖረን ይረዳል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለመገንባት እንደሚያስችልም ማብራራታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ይህን በመገንዘብም መላው የክልሉ ሕዝብ እንደቀድሞው ሁሉ የክረምቱ ወራትን ችግኝ በመትከል እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ግብ ስላልሆነ ከእንስሳት እና ከሰው ንኪኪ ነፃ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የውሃ ሀብትን ለማሳደግ ብሎም የደን ሽፋንን ለመጨመር እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው÷ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር 14 ሚሊየን 950 ሺህ ችግች ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ብለው የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችም የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙና የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.