ጠንካራ የፓርቲ መዋቅር ለመፍጠር የኮሚሽኑ ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራ የፓርቲ መዋቅር ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋናው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ይህን ያሉት የፓርቲው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
ኮሚሽኑን ከማዕከል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ተቋማዊ አቅሙን ለማጠናከር በተደረገው እንቅስቃሴም ጠንካራ የኮሚሽን መዋቅር እየተፈጠረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ በአንዳንድ መዋቅሮች አካባቢ ኮሚሽኑ የፓርቲው ተቋማዊ መዋቅር መሆኑን ከማመን ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ አመለካከቶች እንዲታረሙ፣ በየደረጃው የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ መዋቅር ኮሚሽኑን በሰው ኃይልና በተለያዩ ጉዳዮች መደገፍ እንደሚገባው እና ኮሚሽኑ የሚያቀርበውን ምክረ-ሐሳብ ተቀብሎ መተግበር እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በአጠቃላይ 1ኛውን የፓርቲ ጉባዔ አቅጣጫ ተከትሎ ጠንካራ የፓርቲ ተቋም ለመፍጠር፣ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማስፈን፣ የአሠራር ግልጽነት እንዲኖር እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ለማበጀት በተደረገው ጥረት ውጤት ማምጣት እንደተቻለና አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።