Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ለ190 ሺህ 347 መዛግብት ዕልባት ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 190 ሺህ 347 መዛግብት ዕልባት አግኝተዋል።

ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት፣ ግልጽነት እና የተጠያቂነት ሥርዓትን ከማጠናከር አንጻር አበረታች ውጤት ማስመዝገቡ ተመላክቷል፡፡

አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የታገዙ በማድረግ እንዲሁም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋርነትን ከማሳደግ አኳያ አመርቂ ውጤት መገኘቱም ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የፌደራል ፍ/ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 38 መሰረት ዳኞች የሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት ክብደትና ውስብስብነትን ግምት ውስጥ በማስገባት በቂ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ተደንግጓል፡፡

በዚህ መሰረትም ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 30 በከፊል ዝግ እንዲሆኑ በተደነገገው መሰረት ፍ/ቤቶች ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ዝግ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ወቅትም በባሕሪያቸው አስቸኳይ የሆኑና ጊዜ የማይሰጡ በዜጎች መብትና በሀገር ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አቤቱታዎችና ለውሳኔ የደረሱ መዛግብትን መርምሮ ውሣኔ የመስጠቱ ሒደት ይቀጥላል፡፡

ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓም ጀምሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ሌሎች ጥያቄዎችም በመደበኛው ችሎት እንደሚስተናገዱ ነው የተገለጸው፡፡

በክረምት የዕረፍት ጊዜ ውሣኔ ያገኙ መዛግብት ደግሞ ከጥቅምት 3 ቀን 2018 እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓም ድረስ ለተከራካሪ ወገኖች በችሎት ይገለጻሉ፡፡

በእነዚህ ቀናት ባለጉዳዮች እንዲቀርቡና ውሣኔያቸውን እንዲሰሙ በስልክ ወይም አጭር የጽሑፍ መልዕክት እስከ መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቁ እንደሚደረግ ፍ/ቤቱ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በቀጣዩ ዓመት ፍ/ቤቶች ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ ዳኝነት በመስጠት የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችንና የአሰራር ክፍተቶች በመለየት በትኩረት እንደሚሰራም ተመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.