2ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።
በመክፈቻ ሥነ ሥስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአየር ንብረት ሳምንቱ “ውይይቶችን ወደ ተግባርና ውጤት መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖችን ወደሚጨበጥ የተግባር ውጤት መቀየር ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ኢዜአ ዘግቧል።
የሀገራትን የልማት ትልሞች እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወደ ተጨበጠ ጠንካራ የለውጥ እርምጃ በማቅረብ ለ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የፖሊሲ ሀሳቦች የሚዘጋጁበት ነው ተብሏል።
በብራዚል ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-30) የጋራ አጀንዳን ለመቅረጽ እንደሚያግዝም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የአፍሪካና ሌሎች ሀገራት መሪዎች የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሚካሄድ ይሆናል።