በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ አገልግሎት ሰጭ ማኅበራት አገልግሎታቸውን የሚያሻሽል አሠራር ዘረጉ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ማኅበራት አገልግሎታቸውን የሚያሻሽል አሠራር መዘርጋታቸው ተገለጸ።
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው እንዳሉት፥ ማኅበራቱ ፓርኩን ከጉዳት ለመጠበቅና የሚሰጡትን አገልግሎት ለማዘመን የሚያስችል የጋራ አሠራር ዘርግተዋል።
የአስጎብኝ፣ የምግብ አብሳይ፣ የፈረስ ጫኝ፣ የሆቴልና ምግብ ቤት አገልግሎት ሰጭ፣ የዕቃ አከራይ ማኅበራት የጋራ አሠራሩን ከመሠረቱት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማኅበራቱ ጥምረታዊ አሠራር በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፣ ድክመቶችን ለመቅረፍና የጎብኝዎችን እርካታ በመጨመር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ያለመ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ በፓርኩ ላይ የሚደርሱና እየደረሱ ያሉ ሰው ሠራሽ አደጋዎችን ለመከላከል ያስችላልም ነው የተባለው።
ከዚህ ቀደም ማኅበራቱ አገልግሎቱን የሚሰጡበት የጋራ አሠራር ስላልነበራቸው፥ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች ተጠያቂ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል።
በፓርኩ ዘጠኝ ማረፊያዎች ያሉ ሲሆን ጥምረቱ በእነዚህ ቦታዎች የተሟላ የውኃና የቁሳቁስ አቅርቦት እንዲኖር እንደሚያስችል አብመድ ዘግቧል።
ባለፈው በጀት ዓመት የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ32 ሺህ 400 የውጭ ሀገራት ዜጎች ተጎብኝቷል።