በግማሽ አመቱ 265 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት270 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 265 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን በሚመለከት ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ዘንድሮ በስድስት ወራት 270 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር በመግለጽ 265 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገባት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ እንዳለው በመጥቀስ በቂ ግብር የማይሰበሰብበት ሀገር ውስጥ በቂ ልማት ማምጣት አይቻልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በበቂ ደረጃ ታክስ እየተከፈለ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ሪፎርም ላይ ቢተባበር መልካም ነው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
አምና የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ ችግር ለመፍታት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ሀገር ውስጥ እንደገባም ተናግረዋል፡፡
ትራንስፖርት፣ቴሌኮምና አይ ሲ ቲ ላይ እንዲሁም ኢትዮጵያ ታምርት ብዙ ለውጥ አምጥቷል ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)÷በቅርቡ የካፒታል ማርኬት ይጀመራልም ነው ያሉት፡፡
በዓለም ላይ በኢኮኖሚ ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ስራ የሚፈልገው ሴክተር አንዱ የገቢ አቅም በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ልክ ማሳደግና ማሻሻል ነው ብለዋል፡፡
ወጪ ንግድን በሚመለከት ከሸቀጦችና ከአገልግሎት 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደተቻለ ጠቅሰው በአምስት ወራት ውስጥ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር አስገብተናልም ብለዋል፡፡
ገቢ ንግድን መተካትና ወጪ ንግድን ማብዛት ላይ አሁንም መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በግማሽ አመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ የስራ እድልም መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ሕገ ወጥ ንግድ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የአቅመ ደካማ ቤት መስራት፣ ምግብ ማጋራት፣ተማሪ መመገብ ላይም መስራት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ሪፎርም ላይ በትኩረት መስራት ይጠይቃል ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡
በሻምበል ምህረት