Fana: At a Speed of Life!

አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ድምፃዊው ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ማረፉ ተገልጿል ።

ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ኢትዮጵያን አትንኳት፣ መሰናበቴ ነው፣ እኔ እወድሻለሁ፣ እንደሐገር አይሆንም፣ አዲስ አበባ፣ ክፈቺውና መስኮቱን፣ ውበትም ይረግፋል፣ የከረመ ፍቅር፣ ቀና ብዬ ሣየው፣ ሣይሽ እሳሳለሁ እና ሌሎች በርካታ ሙዚቃዎችን ለአድማጮች አበርክቷል፡፡

የብዙሃን እናት መጠጊያ የምንላት፤
እማማ ናትና ሀገሬን አትንኳት፤
ባድዋ በማይጨው ጀግኖች የሞቱላት፤
ህጻን ሽማግሌ የተሰየፈላት፤
ደመ መራራና ቁጡነት ያለባት፤
ጎጆዬ ናትና ሀገሬን አትንኳት፤
የብዙሃን እናት መጠጊያ የምንላት፤
እማማ ናትና ሀገሬን አትንኳት፡፡
ዘርዓይ ደረስ ወንዱ በሮም የቆመላት፤
ጀግኞች በጦር ሜዳ ወተው የቀሩላት፤
እኔም በተጠንቀቅ አለሁሽ የምላት፤
ጥቁሯን አፍሪካዊት ሀገሬን አትንኳት፡፡ … በሚል ልብን በሚገዛ ግጥምና ዜማ ኢትዮጵያን ያነሳበትን ሙዚቃ በብዙዎች ልብ ውስጥ የቀረ ነው ይባላል፡፡

የተስገምጋሚ ድምጹ ባለቤት አንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ከ50 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ መቆየቱን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ተናግሯል፡፡

ሦስት አስርት ዓመታት የሚጠጋ እድሜውን በውጭ ሀገር ቢያሳልፍም ዜግነቱን አለመቀየሩን ይህም እንደሚያስደስተው በኩራት ይናገራል፡፡

ምን ያክል ሙዚቃዎችን እንደሰራ በውል አላውቀውም የሚለው ድምጻዊው፥ ለሙዚቃ ያለው ፍቅር የተለየ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን እየገለፀ ፥ ለወዳጅ፣ ዘመድ እንዲሁም አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.